የኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን በአራት ዘርፎች ተከፍሎ ሊዋቀር ነው

በአገሪቱ ብቸኛው የኤሌክትሪክ ኃይል አመንጪና አከፋፋይ ሆኖ ላለፉት 55 ዓመታት ሲሠራ የቆየው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን በአራት ዘርፎች ተከፍሎ እንደገና ሊዋቀር ነው፡፡ የውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኮርፖሬሽኑን አዲስ መዋቅር የሚያጠና የኤክስፐርቶች ቡድን የያዘ የኃይል ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን ፕሮግራም ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት አቋቁሟል፡፡

የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ በቦሌ መድኃኔዓለም አካባቢ በሚገኘው ሮቤል ፕላዛ ቢሮውን ከፍቶ ጥናቱን ጀምሯል፡፡

ጥናቱን የሚያካሂዱት ኤክስፐርቶች ይህንን ጥናት ከመጀመራቸው በፊት የአሜሪካ አማካሪ ኩባንያ በሆነው ኤፒኪው ሥልጠና ተሰጥቷቸዋል፡፡

የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ በጥቂት ወራት ውስጥ ጥናቱን አጠናቆ ወደ መዋቅር ለውጡ ይገባል ተብሎ ዕቅድ የተያዘ ሲሆን፣ የኮርፖሬሽኑ አራት ዋና ዋና ክፍሎች ራሳቸውን ችለው እንደሚደራጁ ታውቋል፡፡

እነዚህም የትራንስሜሽን፣ የኮንስትራክሽን፣ የሰብስቴሽንና የዲስትሪቢዩሽን በመባል ተለይተዋል፡፡ የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትር አቶ አለማየሁ ተገኑ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ጥናቱ ከመጠናቀቁ በፊት ኮርፖሬሽኑ ምን ዓይነት መዋቅር ሊኖው እንደሚችል ከወዲሁ ማወቅ እንደማይቻል ገልጸዋል፡፡

መንግሥት በቅርቡ ባፀደቀው የአምስት ዓመቱ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አገሪቱ የምታመነጨውን የኤሌክትሪክ ኃይል አሁን ካለበት 2,000 ሜጋ ዋት ወደ 8,000 ሜጋ ዋት ከተቻለም 10,000 ሜጋ ዋት ለማድረስ ዕቅድ ነድፏል፡፡

ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ ኮርፖሬሽኑ ሦስት መሠረታዊ ለውጦች ማምጣት አለበት ተብሎ በመታመኑ የኃይል ልማት ዕቅድ ተዘጋጅቶ ፀድቋል፡፡

በዚህ ዕቅድ ላይ እንደተገለጸው፣ የመጀመሪያው ለውጥ በኃይል ዘርፍ የተመዘገበውን ዕድገትና በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ሊኖር የሚችለውን ዕድገት በተገቢው መንገድ የሚያስተናግድ ተቋማዊ አቅም መፈጠር ስላለበት፣ ኮርፖሬሽኑ የዓለም አቀፍ የኃይል ዘርፍ ዕድገትን መሠረት አድርጎ እንደገና መደራጀት ይኖርበታል፡፡

ዕቅዱ በሁለተኛ ደረጃ ያስቀመጠው ኤሌክትሪክ በማመንጨት፣ በማስተላለፍና በማሠራጨት የደንበኞች አገልግሎት አሰጣጥን ጨምሮ የማስፋፊያ ሥራዎችን መሥራት ነው፡፡ ሦስተኛው ደግሞ እነዚህን ከላይ የተጠቀሱትን ሥራዎች በአገር ውስጥ አቅም የሚከናወኑበትን መንገድ ማመቻቸት ናቸው፡፡ በዚህም ዕቅድ መሠረት ለኃይል ዘርፍ የሚያስፈልጉት 80 በመቶ የግንባታ ዕቃዎች በአገር ውስጥ እንዲመረቱ የታቀደ ሲሆን፣ ኮርፖሬሽኑ ይህንን ዕቅድ ለማስፈፀም በቅርብ ከተቋቋመው የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርሟል፡፡

ከ1998 ዓ.ም. ጀምሮ ኮርፖሬሽኑ በኃይል ዘርፍ ብዛት ያላቸው የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶችን ቀርጾ ተግባራዊ አድርጓል፡፡ በዚህም መሠረት ቀደም ሲል ከነበረው የኃይል አቅርቦት አሁን ያለው ብልጫ አለው፡፡

በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ የወጣው የኮርፖሬሽኑ የኃይል ልማት ዕቅድ እንደሚያስረዳው፣ ከ1998 ዓ.ም. በፊት የነበረው ኤሌክትሪክ የማስተላለፍ አቅም ከ7,528 ወደ 84,985 ኪሎ ሜትር ከፍ ብሏል፡፡ የማሠራጫ መስመሮች ርዝመትም ከ25,000 ወደ 126,033 ኪሎ ሜትር ከፍ ብሏል፡፡ የደንበኞች ቁጥር ከ95,307 ወደ 1,896,265 ከፍ ብሏል፡፡ ኤሌክትሪክ ያገኙ ከተሞችና መንደሮች ከ648 ወደ 5,163 ከፍ ብለዋል፡፡

ቀደም ሲል የተሠሩ የኃይል ማስፋፋት ሥራዎችንና ከ2003 ዓ.ም. ጀምሮ የሚካሄዱ መጠነ ሰፊ ሥራዎችን ኮርፖሬሽኑ ይዞ ለመቀጠል ከፈለገ አደረጃጀቱን የግድ መለወጥ አለበት በማለት አቶ አለማየሁ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት አምስት አዳዲስ የኃይል ማመንጫዎችን ግንባታ መጀመር፣ ግንባታቸው በመጠናቀቅ ላይ የሚገኙትን ሦስት የኃይል ማመንጫዎች የማጠናቀቂያ ሥራዎችን ማከናወን፣ በተለይ በሶማሌ ክልል የሚገኙ ከተሞችን የብሔራዊ የኃይል ማስተላለፊያ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድረስ ናፍጣ በሚጠቀሙ ጄኔሬተሮች ኃይል እንዲያገኙ ለማስቻል ዕቅድ ተይዟል፡፡

በ1948 ዓ.ም. ተቋቁሞ በልዩ ልዩ መጠሪያዎች ሲጠራ የነበረው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን፣ የአሁኑን ስያሜ ያገኘው በ1998 ዓ.ም. ሲሆን፣ ከዚያ በፊት ደግሞ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክና መብራት ኃይል ባለሥልጣን ይባል ነበር፡፡ ዘንድሮ ጥናቱ ተጠናቆ እንደገና ሲዋቀር ምን ስያሜ እንደሚኖረው የታወቀ ነገር የለም፡፡

_______________________________________________________

Source:

Ethiopian Reporter

Comments
One Response to “የኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን በአራት ዘርፎች ተከፍሎ ሊዋቀር ነው”
  1. kulfo says:

    that sounds good move!

    The decentralization might give a chance for works getting little attention to be considered seriously.
    Do it professionally in such a way that will open a new era in the Ethiopian power industry.

Leave a comment