በአዳማ ከቻይና ባንክ በተገኘ ከ99 ሚሊዮን ዶላር በላይ ብድር የንፋስ ኃይል ማመንጫ ሊገነባ ነው

ከአዳማ ከተማ ሦስት ኪሎ ሜትር ወጣ ብሎ በሚገኝ በተለይ 51 ሜጋ ዋት ማመንጨት የሚችል የንፋስ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ለመገንባት ከቻይና ባንክ ጋር የ99 ሚሊዮን 450 ሺሕ ዶላር የብድር ስምምነት ተፈጸመ፡፡ የተወካዮች ምክር ቤት በትናትናው ዕለት ያጸደቀው የብድር ውል ከቻይና ኤምፖርት ኤክስፖርት ባንክ የተገኘ ሲሆን፣ በ20 ዓመታት እንዲከፈል ስምምነት የተደረገበትና የሰባት ዓመታት የችሮታ ጊዜን ያካተተ ነው፡፡

በአዳማ ለሚተከለው ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በተደረገ ጥናት፣ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ጣቢያው በሚገነባበት ቦታ፣ በ65 ሜትር ከፍታ ላይ በመሆኑ በዓመት የሚገኘው አማካይ የንፋስ ፍጥነትና የንፋስ ኃይል ጥንካሬው የታቀደውን መጠን የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት እንደሚያስችል ተረጋግጧል፡፡

የንፋስ ኃይል ማመንጫው ፕሮጀክት ጠቅላላ ወጪ 123 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ ባንኩ በሰጠው ብድር የተቀመጡ ግዴታዎች መካከል በብድር ከተገኘው ገንዘብ ውስጥ ቢያንስ 50 በመቶ ከቻይና ለሚገዙ እቃዎች፣ ቴክኖሎጂዎችና አገልግሎቶች መዋል ይኖርበታል ይላል፡፡ በተጨማሪም በየዓመቱ የሁለት በመቶ ወለድና የተሰጠው ብድር ገንዘብ ሥራ ላይ እስከሚውል ድረስ፣ ጥቅም ላይ ባልዋለው መጠን ላይ የ0.4 በመቶ የግዴታ ክፍያ ለመክፈል ስምምነት ተገብቷል፡፡

በሌላ በኩል ለከተማ ኃይል ማከፋፈያ፣ ለገጠር ኤሌክትሪክ ኃይል አቅረቦትና ድርጅታዊ አቅምን ለመገንባት መሰረት ባደረገው የኃይል አቅርቦት ፕሮጀክት የ80 ሚሊዮን ዶላር የብድር ስምምነት ከዓለም አቀፍ የልማት ማኅበር ጋር ተፈርሟል፡፡
የልማት ማኅበሩ እ.ኤ.አ በ2002 በሰጠው 130.7 ሚሊዮን ዶላር የኃይል አቅርቦት ፕሮጀክት ተቀርጾ ሲሰራበት የቆየ ነው፡፡

ከዚህ ብድር በተጨማሪነት የተሰጠው 180 ሚሊዮን ዶላር በከተማ የኃይል ማስፋፊያ፣ በገጠር የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት መሻሻያና በአቅም ግንባታ ሥራዎች ለተከፋፈሉ ተግባራት የሚውል ነው፡፡

በከተማ የኃይል ማስፋፊያ ለሚከናወኑ ሥራዎች 137 ሚሊዮን ዶላር በጀት የተመደበ ሲሆን፣ በአዲስ አበባ ያለውን የኤሌክትሪክ ከፍተኛ ኃይል ንዑስ ጣቢያን ከማሻሻል በተጨማሪ ለአዳማ፣ ባህርዳር፣ ድሬዳዋ፣ ደሴ፣ ጂማ፣ መቀሌና ሐዋሳን ለመሳሰሉ ከተሞች የኃይል ማከፋፈያ መረብ እንዲያጠናክሩበት በሚል የተያዘ ነው፡፡

በገጠር የኤሌክትሪክ አቅርቦት በ50 የገጠር መንደሮች ለሚኖሩ 70,000 ያህል ቤተሰቦች የኤሌክትሪክ አገልግሎት የሚያገኝበትና በኦሎቶ ላንጋኖ 35 ሜጋ ዋት የታደሰ ኃይል ለማመንጨት እንዲቻል የተያዘ ግብ ሲሆን፣ 40 ሚሊዮን ዶላር የተመደበለት ነው፡፡

ከዓለም አቀፍ የልማት ማኅበር የተገኘው ይህ ብድር በ40 ዓመታት ሲከፈል የ10 ዓመት የችሮታ ጊዜን እንዲያካትት ውል የተደረገ ሲሆን፣ የ0.75 በመቶ የአገልግሎት ክፍያና የ0.5 በመቶ የግዴታ ክፍያ የሚፈጸምበት የብድር ስምምነት ነው፡፡

በመጪዎቹ አምስት ዓመታት ከ8,000 እስከ 10,000 ሜጋ ዋት የሚደርስ ኃይል ለማመንጨት ዕቅድ ወጥቷል፡፡

____________________________________________________________________________

Source:

Ethiopian Reporter

Leave a comment